Banner

የግእዝ ሥርዓተ ንባብ (Pronunciation)

  • ነሐሴ 19 ቀን 2006 ዓ.ም
  • በመ/ር ደሴ ቀለብ
  • በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር
  • የግእዝ ሥርዓተ ንባብ ስምንት ናቸው፡፡ እነርሱም፡

    1. ማንሳት

    2. መጣል

    3. ማጥበቅ

    4. ማላላት

    5. ማናበብ

    6. አለማናበብ

    7. መዋጥ

    8. መቁጠር ናቸው

    9. ማንሳት፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ሳድስ ከመሆን የተለየ ሆኖ ቃሉ በከፈተኛ ድምፅ የሚነገር ወይም የሚነበብ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የግስ ዓይነቶች በከፍተኛ ድምፅ የተነበቡ ተነሽ ናቸው የሚባሉት፡፡

    ምሳሌ፡- ነበረ = ተቀመጠ

    ሐበነ = ስጠን

    ተዘከረኒ = አስታውሰኝ

    ውእቱ = ነው፣ ነበር፣ እሱ፣ ናቸው ወዘተርፈ፡፡

    አንስት ሖራ = ሴቶች ሔዱ

    ይግበሮ = ይሥራው

    ያጥምቆ = ያጥምቀው

    2. መጣል (ተጣይ)፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ መጨረሻው ሳድስ ሆኖ የማይነሳ ማለት ነው፡፡

    ምሳሌ፡- ማርያም፣ ሚካኤል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ መንግሥት፣ ቅድስት፣ መቅደስ ወዘተርፈ፡፡

    3. ማጥበቅ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ከቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ኖሮ ቃሉ ጠብቆ እንዲነበብ የሚያደርግ ነው፡፡

    ምሳሌ፡- ቀደሰ = አመሰገነ

    ሰብሐ = አመሠገነ

    ተዘከሮ = አስታውሰው

    ነጸረ = ተመለከተ

    4. ማላላት፡- ይህ ሥርዐተ ንባብ በቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ሳይኖርና ንባቡም ላልቶ ሲነበብ ነው፡፡

    ምሳሌ፡- ቀተለ = ገደለ

    ነበረ = ተቀመጠ (ኖረ)

    አምለከ = አመለከ

    ገብረ = ፈጠረ (ሠራ)

    ፈጠረ = ፈጠረ (በአማርኛው ይጠብቃል)

    5. ማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት እንደ አንድ ሆነው ሲናበቡና ን፣ በን ወይም የን ሲያመጡ ነው፡፡

    ምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያን = የክርስቲያን ቤት

    ቤተ መቅደስ = የማመስገኛ ቤት

    ትምህርተ ሃይማኖት = የሃይማኖት ትምህርት

    ድንግለ ሙሴ

    ብሥራተ ገብርኤል

    ዜና ሥላሴ

    ውዳሴ ማርያም

    ጥዑመ ልሳን

    ወልደ ኢየሱስ

    ተዋሕዶ ቃል

    ዜና ቤተ ክርስቲያን

    6. አለማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት ራሳቸውን ችለው ሲነበቡ ወይም አንዱ ላንዱ አጎላማሽ ሲሆን ነው፡፡

    ምሳሌ፡- ቅዱስ አምላክ ይባላል እንጂ ቅዱስ አምላክ አይባልም፡፡

    ድንግል ማርያም

    መጽአ ወልድ – ወልድ መጣ

    ጳውሎስ ሐዋርያ

    7. መዋጥ፡- መዋጥ ማለት ከቃሉ ውስጥ ያለ ፊደል እንዲሁ ሳይጎላ በውስጠ ታዋቂነት የሚነበብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ፊደሉ በጽሑፍ ጊዜ ግን ሥርዓቱን ጠብቆ ይጻፋል፡፡

    ምሳሌ፡- ወይን (wan) ተብሎ እንጂ ወይን (wayyin) ተብሎ አይነበብም፡፡

    ድንግል – ከዚህ ላይ ን ተውጣለች

    ገብር – ከዚህ ላይ ደግሞ ብ ተውጣለች፡፡ ስለዚህ ገብር ባለሁለት ቀለም ነው፡፡

    ኤልሳዕ ከዚህ ላይ ደግሞ ዕ ትዋጣለች፡፡

    ርኩስ ኩ ተውጣለች፡፡

    ከዚህ ላይ ብዙውን ጊዜ የሚዋጡት ቀለሞች ሲሆኑ መዋጥና አለመዋጣቸው ግን እንደ ንባቡና እንደትርጓመው ይለያያል፡፡

    8. መቁጠር፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ በአንድ ቃል ውስጥ የሚገኙ ፊደላትን ያለምንም መዋጥ ማንበብ ማለት ነው፡፡

    ምሳሌ፡– ውእቱ ከሚለው ቃል ሁሉም ፊደላት ይነበባሉ እንጂ ሳድስ ስለሆነች ብቻ የምትዋጥ አይደለችሙ፡፡

    ይእቲ፣ መላእክት፣ ማርያም፣ ማእከል፣ እኅት፣ ትማልም፣ ዮሐንስ፣ አጽፋር (ጥፍሮች) ስእርት (ፀጉር)፣ ኤልያስ፣ ብሔር (ሀገር) እሙንቱ፣ ስብሐት፣ ሐዋርያት፣ መጻሕፍት (ህ ትቆጠራለች)

    ከእነዚህ ሥርዓተ ንባቦች በተጨማሪ ሌሎችም አሉ፡፡

    *** ለምሳሌ፡- ወዳቂና ሰያፍ ***

    *** ሀ. ወዳቂ፡- *** የምንለው ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ካዕብ፣ ሳልስ፣ ራብዕ ኀምስና ሳብዕ ሆኖ የማይነሳ እና ቃሉ ሲነበብ የመጨረሻውን ፊደል በመያዝ እንዲወድቅ የሚያደርግ የሥርዓተ ንባብ ዓይነት ነው፡፡

    *** ምሳሌ፡- *** ኀቤሁ ወደሱ የዚህ ቃል የመጨረሻ ፊደል ሁ ካዕብ ሲሆን ወዳቂ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ልዩነቶች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ውእቱ የሚለው ነባር አንቀጽ ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ እንዲሁም ግሶች በትዕዛዝም ሆነ በሓላፊ ሲመጡ ወዳቂ ናቸው ማለት አንችልም፡፡

    *** ለምሳሌ፡- *** ሖሩ = ሔዱ ወይም ሑሩ = ሒዱ ብንልም ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ ለሣልስ ምሳሌ ከይሲ ብእሲ መዋቲ መሃሪ ወዘተርፈ ሲሆኑ ግስ ከሆነ ግን አይወድቅም፡፡

    *** ምሳሌ፡- *** ሰአሊ ለነ ቅድስት ከዚህ ላይ ሰአሊ የሚለው ቃል ወዳቂ አይደለም ለራብዕ ምሳሌ አንበሳ፣ ዜና፣ ወዘተረፈ ከዚህ ላይም በግስ የሚነገር ከሆነ አይወድቅም፡፡

    *** ለምሳሌ፡- *** እላ አንስት ሖራ /እነዚያ ሴቶች ሔዱ/ ከዚህ ላይ « ሖራ » የሚለው ይነሳል እንጂ አይወድቅም፡፡

    ለኀምስ ምሳሌ ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ይባቤ፣ ወዘተረፈ

    ለሳብዕ ምሳሌ ዶርሆ/ዶሮ/፣ መንበሮ፣ ቀቲሎት/

    ንዑስ አንቀጽ የሆኑት ሁሉ ወዳቂ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ቦዝ አንቀጽ የሆኑ ወዳቂዎች እንዳሉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በግስ ትአዛዝ ወይም ዘንድ አንቀጽ የሆኑት ሊነሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

    *** ፩.፪. የግእዝ ፊደላት አካፋፈል ***

    መጀመሪያ ጊዜ ለሄኖስ በጸፍጸፈ ሰማይ (በሰማይ ገበታነት) የተገለጹለት ፊደላት አሁን በፊደል ገበታ ላይ በቅደም ተከተል እንደምናያቸው ሳይሆን ከዚህ በተለየ መልኩ ተዘበራርቀውና የእብራይስጡን የቋንቋ ስልት ይዘው ነው እነሱም አሌፋት በመባል የራሳቸው ስያሜ ነበራቸው

    አ – አሌፍ ሐ – ሔት ሠ – ሣምኬት

    በ – ቤት ጠ – ጤት ጸ – ጻዴ

    ገ – ጋሜል የ – ዮድ ፈ – ፌ

    ደ – ዳሌጥ ከ – ካፍ ዐ – ዔ

    ሀ – ሄ ለ – ላሜድ ቀ – ቆፍ

    ወ – ዋው መ – ሜም ተ – ታው

    ዘ – ዛይ ነ – ኖን ረ – ሬስ

    በማለት በእብራይስጡ አጠራር ይጠሯቸው ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን የግእዝ ፊደላት በኢትዮጵያ ቀዳማዊ ጳጳስ በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የግእዝ ፊደላትን አሻሽለው አሁን በፊደል ገበታ ላይ የምናያቸውን በቅደም ተከተል ከማስቀመጣቸው በፊት ያሉት ፊደላት፡-

    ቀዳማዊ የግእዝ ፊደላት በሚል ስያሜ የሚጠሩ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከሀ – ጀምሮ በዝርዝር በቀደም ተከተል የምናያቸው ፊደላት ደግሞ ደኀራዊ የግእዝ ፊደላት ብለን በሁለት እንመለከታቸዋለን፡፡

    *** ፩.፫. ቀዳማዊና ደኀራዊ የግእዝ ፊደላት:- ***

    ፩. ቀዳማዊ የግእዝ ፊደላት የምንላቸው በአሁኑ ጊዜ በፊደል ገበታ ላይ አ፣ በ፣ ገ፣ ደ…./አቡጊዳ/ በማለት የምንጠራው የፊደል አቀማመጥ ነው እነዚህ ፊደላት በመነሻ ፊደል ብቻ ነበር የተጻፉት፡፡

    *** ቀዳማዊ የግእዝ ፊደላት ***

    አ የ ረ

    በ ከ ሰ

    ገ ለ ተ

    ደ መ ጰ

    ሀ ነ ፐ

    ወ ሠ ጸ

    ዘ ዐ ፀ

    ኀ ፈ ሐ

    ጠ ቀ

    በዚህ ዓይነት አቀማመጥ በነጠላ በግእዝ ፊደሉ ብቻ ነበር የተቀመጡት ከዚህ በኋላ ግን በእነዚህ ፊደላት ላይ የተወሰኑ ቅጥያዎችን በመጨመር በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህን ፊደላት ወደ ሰባት የፊደላት አዘራዘር በመለወጥ ለእያንዳንዱ ፊደል የተለያዩ ቅርጽና ድምጽን በመፍጠር ፊደላቱ ወደ ሰባት ድምጽ /ሥልት/ ተለውጠው እንዲጻፉ በወቅቱ ከነበሩት ሊቃውንት አባቶች ጋር በመነጋገር የፊደላቱን ቅርጽ አዘጋጅተውልናል፡፡

    ግእዝካዕብሣልስራብዕሐምስሳድስሳብዕ
    ፲፩
    ፲፪
    ፲፫
    ፲፬
    ፲፭
    ፲፮
    ፲፯
    ፲፰
    ግእዝካዕብሣልስራብዕሐምስሳድስሳብዕ
    ፲፱
    ፳፩
    ፳፪
    ፳፫
    ፳፬
    ፳፭
    ፳፮

    ደሐራዊ የግእዝ (የኢትዮጵያ) ፊደላት አጻጻፍ

    ግእዝካዕብሣልስራብዕሐምስሳድስሳብዕ
    ፲፩
    ፲፪
    ፲፫
    ፲፬
    ፲፭
    ፲፮
    ፲፯
    ፲፰
    ፲፱
    ፳፩
    ፳፪
    ፳፫
    ፳፬
    ፳፭
    ፳፮

    የግእዝ ቋንቋ እንደ ሌሎች ቋንቋዎች እራሱን የቻለ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ የሚነገር ጥንታዊ ቋንቋ ነው፡፡ አንድን ቋንቋ እንደ ቋንቋ ከሚያስቆጥሩት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ እና ዋንኛው የራሱ የሆኑ ፊደላት ሲኖሩት እና የራሱን የአነጋገር ሥርዓት ተከትሎ መሄድ ሲችል ነው፡፡ ይህም በመሆኑ በዛሬ አምዳችን ስለ ግእዝ ቋንቋ ፊደላት ብዛትና የፊደላቱንም ስያሜ ትርጒም እንመለከታለን፡፡

    1. የግእዝ ፊደላት አጠቃላይ ብዛት ፳፮ (26) ነው፡፡
    2. የግእዝ ፊደላት በሰባት የአዘራዘር ስልት ይዘረዘራሉ፡፡
    3. የግእዝ ፊደላት ብዛት ከነ አዘራዘራቸው ፻፹፪ (182) ናቸው፡፡
    4. ይህም ማለት እየአንዳንዱ ፊደል በሰባት ሥልት ስለሚዘረዘር ነው፡፡

    ምሳሌ. ሀ. ግእዝ ሁ. ካዕብ ሂ. ሣልስ ሃ. ራብዕ ሄ.ሐምስ ህ.ሣድስ ሆ. ሣብእ ከፊደል ሀ እስከ ፐ ያሉት ፊደላት በዚህ ዓይነት መንገድ ይዘረዘራሉ፡፡

    በፊደል ገበታ ላይ የምናገኛቸው የፊደላት ብዛት አጠቃላይ ፴፫ (33) ሲሆኑ ቀሪዎቹ ፯ (ሰባት) ፊደላት የአማርኛ ፊደላት በመባል ይጠራሉ፡፡ እነዚህን ፊደላት ከነ አዘራዘራቸው በሌላ ጊዜ እናያቸዋለን፡፡ ለዛሬ ፳፮ (26)ቱን የግእዝ ፊደላት በቅደም ተከተል ከነትርጒማቸው እንመለከታለን፡፡

    ፩. ሀ- ብሂል ሀልዎቱ ለአብ እም ቅድመ ዓለም፡፡

    ሀ- ማለት የአብ አኗኗሩ ከዓለም በፊት ነው፡፡

    ፪. ለ- ብሂል- ለብሰ ሥጋ እምድንግል፡፡

    ለ. ማለት- ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ሥጋን ለበሰ፡፡

    ፫. ሐ. ብሂል ሐመ ወሞተ ወተቀብረ፡፡

    ሐ.ማለት ክርስቶስ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፡፡

    ፬. መ. ብሂል መንክር ግብሩ ለእግዚአብሔር፡፡

    መ-ማለት የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው

    ፭. ሠ- ብሂል ሠረቀ በሥጋ፡፡

    ሠ- ማለት ጌታ በሥጋ ተወለደ (ተገለጠ)፡፡

    ፮. ረ- ብሂል ረግዓት ምድር በቃሉ፡፡

    ረ- ማለት ምድር በቃሉ ረጋች (ጸናች)፡፡

    ፯. ሰ- ብሂል ሰብአ ኮነ እግዚእነ፡፡

    ሰ- ማለት ጌታችን ሰው ሆነ፡፡

    ፰. ቀ- ብሂል ቀዳሚሁ ቃል፡፡

    ቀ- ማለት በመጀመሪያ ቃል ነበር፡፡

    ፱. በ- ብሂል በትኅትናሁ ወረደ እግዚእነ፡፡

    በ- ማለት ጌታችን በትሕትናው ወደኛ ወረደ (ተወለደ)፡፡

    ፲. ተ- ብሂል ተሰብአ ወተሰገወ፡፡

    ተ- ማለት ጌታችን ሰው ሆነ፡፡

    ፲፩ . ኀ- ብሂል ኀያል እግዚአብሔር፡፡

    ኀ- ማለት እግዚአብሔር ኀያል ነው፡፡

    ፲፪. ነ- ብሂል ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፡፡

    ነ- ማለት ጌታችን ደዌያችንን ያዘልን ሕመማችንን ተሸከመልን

    ፲፫. አ- ብሂል አአኲቶ ወእሴብሖ ለእግዚአበሔር አቀድም (አእኲቶቶ ለእግዚአብሔር)

    አ- ማለት እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ አመሰግነዋለሁ (እግዚአብሔርን ማመስገንን አስቀድማለሁ)፡፡