ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ጥቅምት ፳፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
እንደዚህ እንደኛ ያለ ክፉ ዘመን የገጠማቸው፣ መጥፎውን ትቶ በጎውን፣ ጠማማውን ሳይሆን ቀናውን፣ የጨለማውን ሳይሆን የብርሃኑን ጎዳና የሚያሳያቸው፣ የሚነግራቸውና የሚያስተምራቸው ያጡ፣ ግራ የተጋቡ ሕዝቦችን የተመለከተበትን ነገር እየነገረን ይመስላል ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው ይህንን ኃይለ ቃል የነገረን፡፡ ነቢዩ በዘመኑ፡-
ነቢይ ነውና አስቀድሞ ዛሬ ላይ እኛ እየገጠመን ያለውን ችግር ማለትም በጎውን የሚናገር፣ በጎውን የሚያደርግ፣ በጎን የሚያሳይ ያጣን ብዙዎች መሆናችንን የእኛን ሕይወት ቀድሞ ታይቶት የነገረንም ነው፡፡
በዘመናችን ብዙዎች ግራ ተጋብተዋል፤ የቀናው መንገድ በጎው ነገር ሁሉ ጠፍቶባቸዋል፤የተሻለውን, የሚጠቅመውን ዕረፍት ሰላም የሚሰጠውን, በጎውን ሁሉ የሚያሳይ በማጣት የሚሠቃዩ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል?›› እያሉ ያለ ዕረፍት ይጮኻሉ፡፡
ለመሆኑ በጎ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በጎ የሚባለው ‹‹ማንኛውም መልካምና ጥሩ ሥራ›› እንደሆነ ይናገርና “በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚገኝ፣ እርሱም ከመንፈስ ቅዱስ የሆነ እንደሆነ፣ ሰዎችም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን የሚገልጹበት መሆኑን ያትታል፡፡ በተጨማሪም የበጎነት ምንጭ እግዚአብሔር መሆኑን ይጠቅሳል፡፡” (መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃለት፣ ገጽ ፻፲፪)