ግእዝ ከእስያ ልሳናት ጋር ሲነጻጸር

በዓለም የሥነ ልሳን ጥናት መሠረት የአካድ /የአሦር – አካዳውያን/ ቋንቋ ጥንታዊ ማንነቱ የተረጋገጠው በአንዳንድ የሥነ ጽሑፎች ቅሪት ሲሆን ይህ ቋንቋ በሥነ ልሳን ተማራማሪዎች ዘንድ የምሥራቅ ሴማዊ ልሳን ተብሎ በቅርብ ጊዜ ከተገኘው ከኤብላዊ ቋንቋ ጋር የሚመደብ ነው፡፡ አካድ እና አሦር በመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት የተገለጹ እና ከኖኅ ዘመን በኋላ የታወቁ መካናተ ሥልጣኔ ናቸው፡፡ በሥነ ጽሑፍ መረጃ የአከድ ልሳን 2500 ቅ.ል.ክ. እንደነበረ ይናገራል፡፡ በኋላ በአራም የአራማውያን የተባለው ቋንቋው ራሱን የገለጸበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በሥነ ቅሬተ ምድርም ሆነ በሥነ ልሳን ተመራማሪዎች ዘንድ አካድ የኢኮኖሚ፣ የሕግ የአስተዳደር፣ የታሪክና የሥነ ጽሑፍ መረጃዎች እንደነበረው የተረዳ ነው፡፡

 የካምም ልጆች ኩሽ፣ ምጽ/ስ/ ራይም፣ ፋጥ፣ ከነዓን ናቸው፡፡ የኩሽም ልጆች ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ሬጌም፣ ሰበቅታ ናቸው፡፡ የሬጌም ልጆችም ሳባ፣ ድዳን ናቸው፡፡ ኩሽም ናምሩድን ወለደ፣ እርሱም በምድር ላይ ኃያል መሆን ጀመረ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት ኃያል አዳኝ እንደናምሩድ ተባለ፡፡ የግዛቱም መጀመሪያ በሰናኦር አገር በባቢሎን አሬክን አርካድ ሌድን ናቸው፡፡ አሦርም ከዚያች አገር ወጣ፡፡ ነነዌን የረሆቦት የተባለችውን ከተማ ካለህን በነነዌና በካለህ መካከልም ሬሴንን ሠራ፡፡ እርስዋም ታላቂቱ ከተማ ናት ምጽራይምም ሉዲምን ኢኒሜቲምን ላህቢምን ነፍታሌምን ጳጥሮሰኒምን ከእነርሱ የፍልስጥኤም ሰዎች የወጡባቸውን ከሳሎሂምን ቀፍቶሪምንም ወለደ፡፡ ዘፍ. 10፡6-14

አፍሪካዊያንም በየዘመናቱ የሥልጣኔ ማእከሉን በወንዞች ጤግሮሰ እና ኤፍራጥስ ዳር እንደ መሠረቱ ፤ አካዳውያን ፈለገ ግዮንን የራሱን ለአፍሪካውያን ሕዝቦች የሥልጣኔ መሠረት አድርጎ መቆየቱ የሚታወስ ታሪክ ነው፡፡ አፍሪካውያን በራሳቸው ፊደል ቢጠቀሙም በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ተጽዕኖዎች ሥር በመውደቃቸው መሠረታዊውን ፊደል ጽሕፈታቸውንና ቋንቋቸውን ሊያጡ ችለዋል፡፡ ይህንን ፊደል ጠብቃ የተገኘችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ፊደልና ቋንቋም በሥነ ጽሑፍ መረጃነት ለዓለም ከቀረቡት ልሳናት የሚታወቅባቸው ባሕርያት ሲኖሩት ከጠፋው ከአካድ ቋንቋ ይብልጥ በሥነ ጽሑፍ መረጃነቱ ራሱን ያሳደገ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህንም በቋንቋው ጠባያት ከአካድ ጋር ቢመሳሰል በራሱ ደግሞ ከአፍሮ እስያ ከቋንቋ መለየት ይህ ሴማዊና ካማዊ ብሎ ለመጠቅለል የሚያስቸግር ቢሆንም በቋንቋ ጥናት ዋና የመለያ ፍጥረት በማጥናት መመደብ የሚቻል ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ግእዝን ሴማዊ፣ ደቡብ ሴማዊ፣ ሰሜን ሴማዊ /በኢትዮጵያ/ አድርገው የሚከፋፍሉበት፡-
– ልዩ ልዩ አስማተ መካናት መመሳሰል ምሳሌ- ሳባ
– የቋንቋዎቹ የራሳቸው መመሳሰል
– የሥነ ቅርጽ መመሳሰል ወዘተ ሲሆን ግእዝ ከነዚህ ቋንቋዎች መደብ የሚለዩት ጠባያት አልነበሩትም፡፡ ወይም ደግሞ በእነዚህ ቋንቋዎች የተዘነጉ ጽሑፎች በግዕዝ ግን አልነበሩም ማለት አይቻልም፡፡ ለአብነትም ያህል «ተስዐቱ» የሚለው የጥንት ሥርው ምን ይመስላል የሚለው ሲጠና ከአረማይክ ይልቅ የግእዝ «ታስዕ» የሚለው ቃል ቀዳሚነት ጥንታዊነት ይኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አረማይክ ያጣውን ግእዙ በመጠበቅ እንዴት አረማይኩ ለግእዝ በዘመኑ ያጣን ቃል ሊያቀብለው ቻለ የሚል ጥያቄ አስነሥቷል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግእዝ በድምጸ ንባቡ የለሌሎች የአፍሪካ ልሳናት እና የሩቅ ምሥራቅ ልሳናት የሚታወቁበትን የድምፀት ንበት በመያዝ ከአፍሪካ ልሳናት ጋር ሊያመሳስለው ይችላል፡፡
ምሳሌ፡
                ቀዳማይ     –     ካልአይ
አካድያን  –     ያቅቱል       –     ያቀትል
ዐረበኛ    –     ቀተለ         –     ያቀቱል
ግእዝ     –     ቀተለ         –     ይቀትል
   
ማስታወሻ- አካድያን ያቅትል ሲል በ «ይ»እና በ «ቅ» መካከል አናባቢ«አ»ኔ ሲጨምር ግእዙ ግን አይጨምርም፡፡ በተጨማሪም በግእዝ ቋንቋ በቀዳማይ አንቀጽ ዝርዝር ጊዜ የአገናዛቢ ቅጥያዎችን የምንጨምር ሲሆን አካድያን ግን የሰማዊነት ባሕርይን የሚያሳይ ነው፡፡Read More

ግእዝ ሥርዓተ ንባብ

የግእዝ ሥርዓተ ንባብ (pronounciation)

ነሐሴ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.
በመ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር
የግእዝ ሥርዓተ ንባብ ስምንት ናቸው፡፡ እነርሱም፡- 
ማንሳት                       5. ማናበብ
መጣል                       6. አለማናበብ
ማጥበቅ                      7. መዋጥ
ማላላት                      8. መቁጠር ናቸው፡፡
1. ማንሳት፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ሳድስ ከመሆን የተለየ ሆኖ ቃሉ በከፈተኛ ድምፅ የሚነገር ወይም የሚነበብ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የግስ ዓይነቶች በከፍተኛ ድምፅ የተነበቡ ተነሽ ናቸው የሚባሉት፡፡
ምሳሌ፡- ነበረ = ተቀመጠ
ሐበነ = ስጠን
ተዘከረኒ = አስታውሰኝ
ውእቱ = ነው፣ ነበር፣ እሱ፣ ናቸው ወዘተርፈ፡፡
አንስት ሖራ = ሴቶች ሔዱ
ይግበሮ = ይሥራው
ያጥምቆ = ያጥምቀው
2. መጣል (ተጣይ)፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ መጨረሻው ሳድስ ሆኖ የማይነሳ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ፡- ማርያም፣ ሚካኤል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ መንግሥት፣ ቅድስት፣ መቅደስ ወዘተርፈ፡፡
3. ማጥበቅ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ከቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ኖሮ ቃሉ ጠብቆ እንዲነበብ የሚያደርግ ነው፡፡
ምሳሌ፡- ቀደሰ = አመሰገነ
ሰብሐ = አመሠገነ
ተዘከሮ = አስታውሰው
ነጸረ = ተመለከተ
4. ማላላት፡- ይህ ሥርዐተ ንባብ በቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ሳይኖርና ንባቡም ላልቶ ሲነበብ ነው፡፡
ምሳሌ፡- ቀተለ = ገደለ
ነበረ = ተቀመጠ (ኖረ)
አምለከ = አመለከ
ገብረ = ፈጠረ (ሠራ)
ፈጠረ = ፈጠረ (በአማርኛው ይጠብቃል)
5. ማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት እንደ አንድ ሆነው ሲናበቡና ን፣ በን ወይም የን ሲያመጡ ነው፡፡
ምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያን = የክርስቲያን ቤት
ቤተ መቅደስ = የማመስገኛ ቤት
ትምህርተ ሃይማኖት = የሃይማኖት ትምህርት
ድንግለ ሙሴ
ብሥራተ ገብርኤል
ዜና ሥላሴ
ውዳሴ ማርያም
ጥዑመ ልሳን
ወልደ ኢየሱስ
ተዋሕዶ ቃል
ዜና ቤተ ክርስቲያንRead More


6. አለማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት ራሳቸውን ችለው ሲነበቡ ወይም አንዱ ላንዱ አጎላማሽ ሲሆን ነው፡፡
ምሳሌ፡- ቅዱስ አምላክ ይባላል እንጂ ቅዱስ አምላክ አይባልም፡፡
ድንግል ማርያም
መጽአ ወልድ – ወልድ መጣ
ጳውሎስ ሐዋርያ
7. መዋጥ፡- መዋጥ ማለት ከቃሉ ውስጥ ያለ ፊደል እንዲሁ ሳይጎላ በውስጠ ታዋቂነት የሚነበብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ፊደሉ በጽሑፍ ጊዜ ግን ሥርዓቱን ጠብቆ ይጻፋል፡፡
ምሳሌ፡- ወይን (wan) ተብሎ እንጂ ወይን (wayyin) ተብሎ አይነበብም፡፡
ድንግል – ከዚህ ላይ ን ተውጣለች
ገብር – ከዚህ ላይ ደግሞ ብ ተውጣለች፡፡ ስለዚህ ገብር ባለሁለት ቀለም ነው፡፡
ኤልሳዕ ከዚህ ላይ ደግሞ ዕ ትዋጣለች፡፡
ርኩስ ኩ ተውጣለች፡፡
ከዚህ ላይ ብዙውን ጊዜ የሚዋጡት ቀለሞች ሲሆኑ መዋጥና አለመዋጣቸው ግን እንደ ንባቡና እንደትርጓመው ይለያያል፡፡
8. መቁጠር፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ በአንድ ቃል ውስጥ የሚገኙ ፊደላትን ያለምንም መዋጥ ማንበብ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ፡– ውእቱ ከሚለው ቃል ሁሉም ፊደላት ይነበባሉ እንጂ ሳድስ ስለሆነች ብቻ የምትዋጥ አይደለችሙ፡፡
ይእቲ፣ መላእክት፣ ማርያም፣ ማእከል፣ እኅት፣ ትማልም፣ ዮሐንስ፣ አጽፋር (ጥፍሮች) ስእርት (ፀጉር)፣ ኤልያስ፣ ብሔር (ሀገር) እሙንቱ፣ ስብሐት፣ ሐዋርያት፣ መጻሕፍት (ህ ትቆጠራለች)
ከእነዚህ ሥርዓተ ንባቦች በተጨማሪ ሌሎችም አሉ፡፡
 
ለምሳሌ፡- ወዳቂና ሰያፍ
ሀ. ወዳቂ፡- የምንለው ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ካዕብ፣ ሳልስ፣ ራብዕ ኀምስና ሳብዕ ሆኖ የማይነሳ እና ቃሉ ሲነበብ የመጨረሻውን ፊደል በመያዝ እንዲወድቅ የሚያደርግ የሥርዓተ ንባብ ዓይነት ነው፡፡
ምሳሌ፡- ኀቤሁ ወደሱ የዚህ ቃል የመጨረሻ ፊደል ሁ ካዕብ ሲሆን ወዳቂ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ልዩነቶች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ውእቱ የሚለው ነባር አንቀጽ ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ እንዲሁም ግሶች በትዕዛዝም ሆነ በሓላፊ ሲመጡ ወዳቂ ናቸው ማለት አንችልም፡፡
 
ለምሳሌ፡- ሖሩ = ሔዱ ወይም ሑሩ = ሒዱ ብንልም ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ ለሣልስ ምሳሌ ከይሲ ብእሲ መዋቲ መሃሪ ወዘተርፈ ሲሆኑ ግስ ከሆነ ግን አይወድቅም፡፡
 
ምሳሌ፡- ሰአሊ ለነ ቅድስት ከዚህ ላይ ሰአሊ የሚለው ቃል ወዳቂ አይደለም ለራብዕ ምሳሌ አንበሳ፣ ዜና፣ ወዘተረፈ ከዚህ ላይም በግስ የሚነገር ከሆነ አይወድቅም፡፡
 
ለምሳሌ፡- እላ አንስት ሖራ /እነዚያ ሴቶች ሔዱ/ ከዚህ ላይ « ሖራ » የሚለው ይነሳል እንጂ አይወድቅም፡፡
ለኀምስ ምሳሌ ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ይባቤ፣ ወዘተረፈ
ለሳብዕ ምሳሌ ዶርሆ/ዶሮ/፣ መንበሮ፣ ቀቲሎት/
ንዑስ አንቀጽ የሆኑት ሁሉ ወዳቂ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ቦዝ አንቀጽ የሆኑ ወዳቂዎች እንዳሉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በግስ ትአዛዝ ወይም ዘንድ አንቀጽ የሆኑት ሊነሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ 

ሰዋስወ ግእዝ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በቅድሚያ በሕያውና ዘለዓለማዊ በሆነ በእግዚአብሔር ስም የከበረ ሰላምታዬን እያቀረብኩ ስለ ግእዝ ቋንቋ አጠር ባለ መልኩ እገልጻለሁ፡፡

የግእዝ ቋንቋ ቀዳማዊነት

ቋንቋ ማለት መግባቢያ መተዋወቂያ መነጋገሪያ አሳብ ለአሳብ መገላለጫ ወዘተ…… ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ባለበት ቦታ ሁሉ ቋንቋ አለ፤ ቋንቋም ባለበት ቦታ ሕዝብ አለ፤ ያለ ሕዝብ ቋንቋ ያለ ቋንቋ ሕዝብ ሊኖር አይችልም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ ስለ ግእዝ ቋንቋ አመጣጥ አጠር ባለ መልኩ ስንነጋገር፡-

ከአንዳንድ ቀደምት የታሪክ ጸሐፊዎችና የግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፈው ካስረከቡን ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና የቋንቋው ባለቤቶች እንደምንረዳው፡- የግእዝ ቋንቋ አመጣጥ በኢትዮጵያ መነሻ ሊሆነን የሚችለው ከስምንተኛው ምዕተ ዓመት ቅድመ ልደት ክርስቶስ ጀምሮ ነገደ ሴም /የሴም ዘሮች/ወገኖች/ ቋንቋቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ሴማዊ ቋንቋ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ቋንቋ ሆነ፡፡ ነገደ ሴም ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ቋንቋቸውን በመግባቢያነት አሳድገው፣ ሥነ ጽሑፋቸውን አስፋፍተው፣ በባቢሎን በአካድና፣ በአሶር ይኖሩ ነበር፡፡ በኋላ ግን ለሁለት ተከፍለው ግማሾቹ ሴማውያን ሰሜንና ምስራቅ እስያን፣ ግማሾቹ ሴማውያን ደግሞ ደቡቡ እስያን ይዘው ይኖሩ ነበር፡፡

የሰሜን እስያ ሴማውያን ቋንቋ /የአካድ ቋንቋ/ አማራይክ፣ ዕብራይስጥንና ፊንቄን ሲያስገኝ የደቡብ እስያ ሴማውያን ቋንቋም /አካድ ቋንቋ/ ሳባን ግእዝንና የተለያዩ በኢትዮጵያ ውስጥ በመግባቢያነት የምንጠቀምባቸውን ሴማውያን ቋንቋዎች አስግኝቷል፡፡ በደቡብ እስያ ይኖሩ የነበሩ ነገደ ሴም በተለያየ ምክንያት እየፈለሱ ወደ ደቡብ ዐረብ፣ ወደ የመንና ወደ አካባቢዋ መጥተዋል ከዝያም ፈልሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአክሱምና በአካባቢዋ ሰፍረው ይዘዋቸው ከመጡት ቋንቋዎቻቸው መካከል በታሪክ ጎልተው የሚታወቁና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓትም በአገልግሎት ላይ የሚገኙት ቋንቋዎች የሳባ እና የግእዝ ቋንቋዎች ናቸው፡፡

ነገደ ሴም /ሴማውያን/ ቋንቋዎቻቸውን /ሳባና ግእዝን/ ከነገደ ካም ቋንቋ ጋር አስማምተው በመያዝ ሁሉንም ቋንቋዎች ሲናገሩዋቸው ኖረው ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳባና ግእዝ እየተለመዱና እየተስፋፉ እየዳበሩም ከመሄዳቸው የተነሣ የነገደ ካምን ቋንቋ እየዋጡት መጥተው ሁለቱ ሳባ እና ግእዝ ቋንቋዎች ብቻ ሀገራዊ ቋንቋዎች ይሆኑ ጀመር እየቆዩ ግን ሁለቱ /ሳባና ግእዝ/ በጣም ተመሳሳይና ተቀራራቢ በመሆናቸው እንደ አንድ ቋንቋ ሆነው ይነገሩ ጀመር፡፡ ይኸም ጽሑፉ /ፊደሉ/ በሳባ እንዲጻፍ እና መነጋገሪያ ቋንቋውን ደግሞ በግእዝ እንዲሆን በመደረጉ ነው፡፡ ነገደ ሴም በሳባ ቋንቋቸው ሳባውያን፣ በግእዝ ቋንቋቸው ደግሞ አግአዝያን ተብለው የሚጠሩት ከዚህ መነሻነት ነበር፡፡

ለዚህም መረጃ የሚሆኑን ሳባና ግእዝ ቋንቋዎች ተጽፈውባቸው የሚገኙት ጥንታውያን የኢትዮጵያ ቅርሶች እንደ የአክሱምና የላሊበላ ሐውልቶች በየሐ እና በአዱልስ ወዘተ….. የተለያዩ በድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ቅርጻ ቅርጾች እስከ አሁን ቆመው የሚገኙ የዚህ ቋሚና ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ የሳባና የግእዝ ቋንቋዎች በዚህ ሁኔታ እስከ 324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. አካባቢ ድረስ አብረው ሲነገሩ ቆይተዋል በኋላ ግን የሳባ ንቋ እየተዳከመና በግእዝ ቋንቋ እየተዋጠ ይሄድ ጀመር እንደ ምንም እየተንገዳገደ እስከ 350 /፫፻፶/ ዓ.ም. ቆይቶ ከዚህ በኋላ ከሥነ – ጽሑፍ ከመነጋገሪያነትም ፈጽሞ ቀረ የግእዝ ቋንቋ ግን ከ324 /፫፻፳ወ፬/ዓ.ም. ጀምሮ ብቸኛ ሀገራዊ ቋንቋ በመሆን እስከ ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም የአማርኛ ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ሲያገለግል እንደ ነበር የታሪክ ጸሐፊዎች በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡ 

Read More

መዝገበ ቃላት

የግስ ምንነት

ግስ ከቃል ክፍሎች አንዱ ሲሆን በብዙ መንገድ ሊፈታ ይችላል። በዋናነት ግን ድርጊት አመልካች የሆነ በዐረፍተ ነገር ውስጥ የሐሳብ መደምደሚያ፣ ወይም የዐረፍተ ነገር ማሠሪያ ተብሎ ይተረጎማል። በርካታ ምሁራን በተለያየ መልኩ ስላብራሩት የምሁራኑን አገላለጽ እንደሚከተለው እንመልከት።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው እንዲህ ያስረዳሉ።

ግስ ፡- መግሰስ፣ አንዱን ቃል ማርባት፣ ማብዛት፣  የሩቁን  ለቅርብ፣  የወንዱን ለሴት፣ ያንዱን ለብዙ መስጠት፣  ማወራረስ፣  የቅኔ፣ የዚቅ፣ የወረብ፣ የለዘብ።

ግስ፡- ጓዝ፣ እክት፣ ግስንግስ ፣ ዕቃ፣ ግሴት የሚያዝና፣ የሚዳሰስ ኹሉ፣

ግስ፡- በቁሜሙ፣ የቋንቋ መጣፍ፣ የዘርና የነባር መድበል፣ መዝገበ ቃል፣ ንባቡ በፊደል ተራ የታከተ፣ የተከተተ። ምሥጢሩ ግን ተወራራሽ ቃል ማለት ነው። አንዱ አንቀጽ እስከ ሰማንያ ነባሩና ጥሬው እስከዐሥር መርባቱ በመወራረስ ነውና። (ኪዳነ ወልድ፣ ገጽ ፫፻፴፫-፫፻፴፬)

አለቃ ኪዳነ ወልድ በተለያየ አገላለጽ ቢገልጹትም በዋናነት ግን ግስ አንቀጽን ማርባት፣ መግሰስ፣ ጓዙን ማሳየት ወዘተ ማለት እንደሆነ እንረዳለን። በሌላ በኩል የአማርኛ ሰዋስውን በስፋት ያጠኑት ፕሮፌሰር ባየ ይማም ደግሞ የአማርኛ ሰዋስው በሚል መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ያስረዳሉ።

ግስ፡- ማንኛውም በዐረፍተ ነገር መድረሻ ላይ ሊገባ የሚችልና እንደ /-ሁ/፣/-ህ/ ፣/-ሽ/ ወዘተ ያሉ መደብ አመልካች ምዕላዶችን ሊያስከትል የሚችል ቃል ሁሉ ግስ ተብሎ በዚህ ክፍል ውስጥ ሊመደብ ይችላል። (ባየ.ገጽ ፹፬) ይሉንና በሌላኛው ገጽ ደግሞ

ግሶች ለመደብ፣ ለጾታ ፣ለቍጥር፣ ለአንቀጽ፣ ለስልት፣ እንዲሁም ለጊዜ የተለያዩ ቅጣይ ምዕላዶችን፣ በማስቀደም ወይም በማስከተል ቅድመ መድረሻ ተናባቢያቸውን በማጥበቅ ወይም ባለማጥበቅ እንዲሁ ከተለያዩ ረዳት ግሶች ጋር በመጣመር ቅርጻቸውን ሊለዋውጡ ይችላሉ። (ባየ.ገጽ.፻፴፫) በማለት ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ባየ ይማም ከመዋቅር አንጻር በአማርኛ ስለተመለከቱት እንጂ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከግእዝ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ምክንያቱም በአማርኛ መዋቅር ግስ ወይም ማሰሪያ አንቀጽ ከዐረፍተ ነገር መጨረሻ ስለሚገባ ነው። በግእዝ ቋንቋ ግን በመጀመሪያም በመጨረሻም ሊገባ ይችላል። ሌላው መስፈርት ግን በመደብ፣ በጾታ በቁጥር ወዘተ መብዛቱና መደብ፣ ጾታ እና ቍጥር አመልካች ምዕላድ ማስከተሉ በሁለቱም ቋንቋ ተመሳሳይነት አለው። ምን አልባት አመልካች ምዕላዶች ይለያዩ ካልሆነ በቀር። ከላይ በኪዳነ ወልድ አገላለጽ የተመለከትነውም ማርባት፣ ማብዛት፣ መግሰስ ወዘተ የተባለው ይህን የሚያስረዳ ነው።

መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በሚል መጽሐፋቸው ግስን እንደሚከተለው ገልጸውት እናገኛለን።

ግስ ድርጊትንና ሁኔታን የሚገልጽ የቋንቋ መዝገበ ቃል የምሥጢር መፍቻ ቁልፍ ነው። (አስበ ድንግል፣ገጽ፴፭)

ሌላው መምህር ዕንባቆም ገብረ ጻድቅ የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ በሚል መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውት እናገኛለን።

ግስ ማለት ጌሰ፤ ገሰገሰ፤ ተራመደ፤ ተስፋፋ፣ ከሚለው ግስ የተገኘ ዘመድ ዘር ሲሆን የአንድ ዐረፍተ ነገር (ኃይለ ቃል) ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን ዐረፍተ ነገሩ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርግ ነው።

ግስ ማለት፡- ገሰሰ ዳሰሰ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ሲሆን የቃላት መራቢያ፣ ገስጋሽ፣ ተመላላሽና ተወራራሽ ቃል ነው። (ዕንባቆም፣፴፭)

ከመምህር ዕንባቆም አገላለጽም የምንረዳው ከላይ በተመለከትነው መሠረት ግስ የዐረፍተ ነገር ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን የሚያገልግል፣ የሐሳብ መቋጫ የሚሆን፣ በብዙ መንገድ የሚረባ የቃላት ሁሉ መነሻ ማለት እንደሆነ ነው።

በሌላ መልኩ አንዳንድ መምህራን ግስን አንቀጽ በሚል ስያሜ ይጠሩታል።

አንቀጽ፡- የአድራጊ፣ የድርጊትና የሁኔታ፣ አንድና ብዙ ቍጥርን፣ ቅርብና ሩቅ መደብን፣ ተባዕታይና አንስታይ ጾታን፣ ሐላፊ፣ አሁንታና ትንቢት ጊዜያትን፣ ወዘተ የሚያስረዳ ቃል አንቀጽ ይባላል። አንቀጽ ማለት መግቢያ፣ መውጫ፣ መመላለሻ በር ማለት ነው።

አንቀጽ የተባለበት ምክንያትም፡- ይህ ዓይነት ቃል “አንቀጽ” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በበር እንደሚገባበት፣ እንደሚወጣበት፣ እንደሚመላለሱበት፣ አእምሮ (ዕውቀት) የጠለቀ ምሥጢርን፣ የረቀቀ ጥበብን፣ ለመረዳት አንቀጽን እየመረመረ በምርምራዊ ሐሳብ ስለሚወጣበት፣ ስለሚገባበት፣ ስለሚመላለስበት ነው።

ጠቅለል ሲደረግ ግስ ድርጊት አመልካች የሆነ፣ በዐሥሩም መራሕያን እየረባ ለብዙ ቃላት መመሥረት መነሻ የሚሆን፣ መደብን ፣ ቍጥርን፣ ጾታን የሚያመለክቱ ምዕላዶችን እየጨመረ በልዩ ልዩ መልኩ የሚረባ ቃል ማለት ነው። አንቀጽ መባሉ አንቀጽ መግቢያ በር ማለት ሲሆን ግስም ቃላትን ለመመሥረት መነሻና መጀመሪያ በመሆን ስለሚያገለግል ነው።

የግስ ዓይነት፡-

የግስ ዓይነት ሲባል በልዩ ልዩ መልኩ ልንመለከተው እንችላለን።  ይህም ከአርእስት አንጻር፣ ከመሳብና ካለመሳብ አንጻር፣ ልንመለከተው እንችላለን።

ከአርእስት አንጻር ስንመለከተው ስምንት ናቸው። ከመሳብና ካለመሳብ አንጻር ስንመለከተው ደግሞ ሁለት ናቸው ። እነርሱም ገቢርና ተገብሮ ይባላሉ። እንዲሁም ዘር አንቀጽና  ነባር አናቅጽ ተብለውም በሁለት ይከፈላሉ። እያንዳንዱን ከምሳሌ ጋር እንመለከተዋለን።

ገቢርና ተገብሮ ግስ

ገቢር ግስ፡- ይህ ማለት ባለቤት አድራጊ የሆነበትና ግሱ ተሳቢ የሚፈልግ ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ዳዊት ቀተለ ጎልያድሀ ቢል ዳዊት ጎልያድን ገደለ ማለት ነው። በዚህ ዐረፍተ ነገር ባለቤቱ ዳዊት ነው አድራጊ ነው። ግሱ ቀተለ ነው ተሳቢ ጎልያድን የሚፈልግ ወይም የሚሻ ማለት ነው።

ተገብሮ ግስ፡- ባለቤቱ ድርጊቱ የሚፈጸምበትና ግሱ ሌላ ተሳቢ የማይፈልግ ማለት ነው። ለምሳሌ ጎልያድ ተቀትለ ቢል ጎልያድ ተገደለ ማለት ሲሆን ባለቤቱ ራሱ ጎልያድና ድርጊት የሚፈጸምበትም ራሱ ነው ስለዚህ ግሱም ሌላ ተሳቢ አያስፈለገውም።

ዘር አንቀጽና ነባር አናቅጽ

ዘር አንቀጽ ፡-ይህ ማለት  መነሻ አንቀጽ ያለው የሚረባ፣ የሚገሰስ ማለት ነው። ለምሳሌ ቀደሰ፣ ቀተለ፣ ተንበለ፣ ወዘተ. ሲሆን ዘር አንቀጽ በራሱ ዐበይትና ንኡሳን አናቅጽ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። ዐበይት የሚባሉት ራሳቸውን ችለው ማሰር የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽ፣ ሣልሳይ አንቀጽ ናቸው። ንኡሳን አናቅጽ የሚባሉት ግን የግስ ዘር ሁነው ግን ራሳቸውን ችለው ማሠር የማይችሉት ናቸው። ለምሳሌ ዘንድ አንቀጽ፣ ውስጠ ዘ፣ ሳቢዘር ወዘተ.

ነባር አንቀጽ፡- ይህ ማለት ደግሞ የሚረባ ግስ የሌለው በራሱ ማሰሪያ አንቀጽ የሚሆን ማለት ነው። ለምሳሌ ውእቱ፣ አልቦ፣ አኮ፣ ቦ ወዘተ

ውድ አንባብያን እያንዳንዱን በሰፊው በሚቀጥለው ክፍል እንመለስበታለን ለአሁኑ ግን እዚህ ላይ ይቆየን።