6. አለማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት ራሳቸውን ችለው ሲነበቡ ወይም አንዱ ላንዱ አጎላማሽ ሲሆን ነው፡፡
ምሳሌ፡- ቅዱስ አምላክ ይባላል እንጂ ቅዱስ አምላክ አይባልም፡፡
ድንግል ማርያም
መጽአ ወልድ – ወልድ መጣ
ጳውሎስ ሐዋርያ
7. መዋጥ፡- መዋጥ ማለት ከቃሉ ውስጥ ያለ ፊደል እንዲሁ ሳይጎላ በውስጠ ታዋቂነት የሚነበብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ፊደሉ በጽሑፍ ጊዜ ግን ሥርዓቱን ጠብቆ ይጻፋል፡፡
ምሳሌ፡- ወይን (wan) ተብሎ እንጂ ወይን (wayyin) ተብሎ አይነበብም፡፡
ድንግል – ከዚህ ላይ ን ተውጣለች
ገብር – ከዚህ ላይ ደግሞ ብ ተውጣለች፡፡ ስለዚህ ገብር ባለሁለት ቀለም ነው፡፡
ኤልሳዕ ከዚህ ላይ ደግሞ ዕ ትዋጣለች፡፡
ርኩስ ኩ ተውጣለች፡፡
ከዚህ ላይ ብዙውን ጊዜ የሚዋጡት ቀለሞች ሲሆኑ መዋጥና አለመዋጣቸው ግን እንደ ንባቡና እንደትርጓመው ይለያያል፡፡
8. መቁጠር፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ በአንድ ቃል ውስጥ የሚገኙ ፊደላትን ያለምንም መዋጥ ማንበብ ማለት ነው፡፡
ምሳሌ፡– ውእቱ ከሚለው ቃል ሁሉም ፊደላት ይነበባሉ እንጂ ሳድስ ስለሆነች ብቻ የምትዋጥ አይደለችሙ፡፡
ይእቲ፣ መላእክት፣ ማርያም፣ ማእከል፣ እኅት፣ ትማልም፣ ዮሐንስ፣ አጽፋር (ጥፍሮች) ስእርት (ፀጉር)፣ ኤልያስ፣ ብሔር (ሀገር) እሙንቱ፣ ስብሐት፣ ሐዋርያት፣ መጻሕፍት (ህ ትቆጠራለች)
ከእነዚህ ሥርዓተ ንባቦች በተጨማሪ ሌሎችም አሉ፡፡
ለምሳሌ፡- ወዳቂና ሰያፍ
ሀ. ወዳቂ፡- የምንለው ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ካዕብ፣ ሳልስ፣ ራብዕ ኀምስና ሳብዕ ሆኖ የማይነሳ እና ቃሉ ሲነበብ የመጨረሻውን ፊደል በመያዝ እንዲወድቅ የሚያደርግ የሥርዓተ ንባብ ዓይነት ነው፡፡
ምሳሌ፡- ኀቤሁ ወደሱ የዚህ ቃል የመጨረሻ ፊደል ሁ ካዕብ ሲሆን ወዳቂ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ልዩነቶች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ውእቱ የሚለው ነባር አንቀጽ ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ እንዲሁም ግሶች በትዕዛዝም ሆነ በሓላፊ ሲመጡ ወዳቂ ናቸው ማለት አንችልም፡፡
ለምሳሌ፡- ሖሩ = ሔዱ ወይም ሑሩ = ሒዱ ብንልም ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ ለሣልስ ምሳሌ ከይሲ ብእሲ መዋቲ መሃሪ ወዘተርፈ ሲሆኑ ግስ ከሆነ ግን አይወድቅም፡፡
ምሳሌ፡- ሰአሊ ለነ ቅድስት ከዚህ ላይ ሰአሊ የሚለው ቃል ወዳቂ አይደለም ለራብዕ ምሳሌ አንበሳ፣ ዜና፣ ወዘተረፈ ከዚህ ላይም በግስ የሚነገር ከሆነ አይወድቅም፡፡
ለምሳሌ፡- እላ አንስት ሖራ /እነዚያ ሴቶች ሔዱ/ ከዚህ ላይ « ሖራ » የሚለው ይነሳል እንጂ አይወድቅም፡፡
ለኀምስ ምሳሌ ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ይባቤ፣ ወዘተረፈ
ለሳብዕ ምሳሌ ዶርሆ/ዶሮ/፣ መንበሮ፣ ቀቲሎት/
ንዑስ አንቀጽ የሆኑት ሁሉ ወዳቂ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ቦዝ አንቀጽ የሆኑ ወዳቂዎች እንዳሉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በግስ ትአዛዝ ወይም ዘንድ አንቀጽ የሆኑት ሊነሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
Copyright @2024 MK US Center| Powered by: Next Generation